ባለፈው ሰኞ ሌሊት፣ ከምትኖርበት ሕንፃ አምስተኛ ፎቅ ላይ ቁልቁል ወድቃ ሕይወቷ ካለፈው፣ ሞዴል እና የማስታወቂያ ባለሞያ ቀነኒ አዱኛ ሞት ጋራ በተያያዘ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የሚገኘው እጮኛዋ አርቲስት አንዱዓለም ጎሣ፣ ተጨማሪ 13 ቀናትን በእስር ቆይቶ ምርመራ እንዲቀጥል ፍርድ ቤት አዘዘ።
የዐዲስ አበባ ፖሊስ፣ ከቀነኒ ሞት ጋራ በዋና ወንጀል አድራጊነት የጠረጠረው አንዱዓለምን እንደኾነ በመግለጽ፣ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ የነበረ ሲኾን፣ ከጠበቃው ጋራ ፍርድ ቤት የቀረበው አንዱዓለም ደግሞ፣ የቀነኒ ሕይወት ያለፈው በአደጋ እንደኾነ በመግለጽ ከእስር እንዲፈታ አመልክቶ ነበር።
ሟች ቀነኒ አዱኛ ዋቆ፣ ሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሌሊቱ 10 ሰዓት ገደማ፣ አምስተኛ ወለል ላይ ከሚገኘው የቤቷ የማብሰያ ክፍል ቨረንዳ በኩል፣ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ኹኔታ ቁልቁል ወደ ምድር ወድቃ ለሕክምና ርዳታ ወደ ያኔት ሆስፒታል እየተወሰደች ባለችበት ወቅት ሕይወቷ ማለፉን፣ የዐዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ትላንት አስታውቆ ነበር።
የምርመራ መዝገቡን ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው ፖሊስ፣ ሞዴል ቀነኒ፥ ሕይወቷ ባለፈበት ወቅት፣ ፍቅረኛዋ አርቲስት አንዱዓለም በቤት ውስጥ እንደነበር ጠቅሶ፣ የአስከሬን ምርመራ ውጤትን ጨምሮ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ ለማቅረብ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ነበር።
"ለምርመራ የሚያበቃ በቂ ምክንያት የለም፤" በሚል ተቃውሞ ማቅረባቸውን ለአሜሪካ ድምፅ የገለጹት፣ የአርቲስት አንዱዓለም ጎሣ ጠበቃ አቶ ሊባን አብዲ ሑሴን፣ የቀነኒ ሕይወት ያለፈው "በአደጋ ነው" የሚል ምላሽ መስጠታቸውን አስረድተዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱ፣ የአስከሬን ምርመራ ውጤትን ጨምሮ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን አጠናቅሮ እንዲያቀርብ፣ ለፖሊስ ተጨማሪ የ13 ቀናትን የጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ፣ ለመጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል።
🔷 የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሊንኮችን በመጫን ይከተሉን።
ፌስቡክ - www.facebook.com/voaamharic
ኢንስታግራም - www.instagram.com/voaamharic
X - www.twitter.com/VOAAmharic
ዌብሳይት - amharic.voanews.com/
የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ፡- youtube.com/voaamharic
☎️የስልክ መሥመራችን 202-205-9942 የውስጥ መሥመር 14 ነው።
📡 ቪኦኤ-አማርኛ ስለ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ አፍሪካ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ዓለም አቀፍ በዲጂታል፣ በራዲዮና በቴሌቪዥን ዜናና ዘገባዎችን ለአድማጭና ለተመልካች ያቀርባል።
VOA Amharic reaches our audience on digital, radio, and TV, delivering news and content about Ethiopia, Eritrea, Africa, and the United States. We will also be bringing you Health Shows, Youth Shows, Democracy Field, Women’s Shows, and Sports Shows on different days, stay tune
コメント